Fana: At a Speed of Life!

የውል እርሻ አርሶ አደሩን እና ባለሃብቱን ባሳተፈ መንገድ በቀጣይ ሊሰራበት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የውል እርሻ አርሶ አደሩን እና ባለሃብቱን ባሳተፈ መንገድ በቀጣይ ሊሰራበት እንደሚገባ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ኃይለማሪያም ከፍያለው ገለጹ፡፡

የውል እርሻ በገበሬዎች እና በማቀነባበሪያ ወይም በግብይት ድርጅቶች መካከል የግብርና ምርቶችን ለማምረት እና ለማቅረብ የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር በአማራ ክልል በግብርና ምርት ውል አመራረት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ፥ የውል እርሻ በዓለም ላይ በግብርናው ዘርፍ ከማምረት እስከ ግብይት ድረስ ውጤታማ ነው ያሉ ሲሆን ፥ በኢትዮጵያ አማራ ክልልም በውል እርሻ አሰራር የተሻለ ተሞክሮ እንዳለው ገልጸዋል።

የውል እርሻ እስካሁን የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ያነሱት ዶክተር ሶፊያ ፥ አሰራሩን በሕግ ለመምራት የውል እርሻ አዋጅ መጽደቁን ገልጸዋል።

አዋጁ ተግባራዊ እስኪሆን አሁን ባለው አሰራር አርሶ አደሩን ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ኃይለማሪያም ከፍያለው ፥ የግብርና አመራረት ውል በክልሉ በአንድ አመት ውስጥ የተሻለ ልምድ የተገኘበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይ አርሶ አደሩን እና ባለሀብቱን በሰፊው ባሳተፈ መንገድ ሊሰራበት የሚገባ አሰራር እንደሆነ አንስተዋል።

ዶክተር ኃይለማሪያም እንዳሉት ፥ አሰራሩ በክልሉ በ2013/14 የምርት ዘመን አራት ዞኖች በሚገኙ አራት ወረዳዎች ጥቂት ሰብሎችን በ13 ሽህ ሄክታር መሬት ላይ ከ130 ሺህ ኩንታል በላይ በማምረት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ድጋፍ ተደርጓል።

እንደ ማሾ ፣ ቦሎቄ እና የመሳሰሉ ሰብሎችንም ለኢንዱስትሪው እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚያስችል መልኩ በሰፊው መሰራቱን ገልጸዋል።

አሰራሩን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በክላስተር የአመራረት ዘዴ በግብርና ምርት ውል ማስተሳሰር ከተቻለ ኢንዱስትሪውን፣ ገበያውን እና የውጭ ምንዛሬውን ማረጋጋት ይቻላል ብለዋል።

በአማራ ክልል በግብርና ምርት አመራረት ውል ላይ የባለ ድርሻ አካላት ውይይት ከጂ አይ ዜድ ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት ድጋፍ ፕሮጀክት እና ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

በኤልያስ አንሙት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.