ኢትዮጵያና ኤርትራ የምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስጋቶች መሆናቸው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስጋቶች መሆናቸውን ጋዜጠኛ ቶማስ ማውንቴን ተናገረ፡፡
ጋዜጠኛ ቶማስ ከአር ቲ ጋር በነበረው ቆይታ እንደተናገረው÷ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የዓለም የንግድ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድበት በመሆኑ የምዕራባውያን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ፍላጎት እየሆነ መምጣቱን አብራርቷል፡፡
በተለይም አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ስታደርግለት የነበረው የህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ÷ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን በወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በበላይነት ስትቆጣጠረው እንደነበር ገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ማስፈናቸውን ተከትሎ አሜሪካ በቀጠናው ያላት የበላይነት እየቀነሰ መምጣቱን ጋዜጠኛው ተናግሯል፡፡
የአሜሪካን የተዘባ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ያልተቀበሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ ከአሜሪካ መንግሥት በርካታ ማዕቀቦች እንደተጣለባቸው ጋዜጠኛ ቶማስ አብራርቷል፡፡
አሜሪካ በቀጠናው ያላትን የበላይነት ለመቆጣጠር አሜሪካ በደኅንነት ተቋሟ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ህዋሓት በተለያዩ ዓለማቀፋዊ ተቋማት በመታገዝ ድጋፍ እያደረገች መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ኩባ የአሜሪካን ማዕቀብ ተቋቁማ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ሀገር ስትሆን÷ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደግሞ ለአሜሪካ ማዕቀብ እጅ ያልሰጡ አፍሪካዊ ሀገራት መሆናቸውን ቶማስ ማውንቴን ገልጿል፡፡
ምዕራባውያን ÷ አፍሪካውያን የእነሱ ተመፅዋች ሆነው እንዲቀጥሉ ይፈልጋሉ ያለው ጋዜጠኛው÷ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ልምድ በመውሰድ ሉዓላዊነታቸውን ማስከብር እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!