አሸባሪውን የሸኔ ቡድን ለማጥፋት ህዝባዊ አንድነት ወሳኝ መሣሪያ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን እየዘረፈ፣ እያሰቃየ እና እየገደለ የሚገኘውን አሸባሪ የሸኔ ቡድን ማጥፋት የሚቻለው በሕዝቡ የተባበረ ክንድ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስታወቀ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታዬ ጉዲሳ እንደገለጹት÷ አሸባሪው ሸኔ በሕዝቡ ውስጥ በድብቅ እየተንቀሳቀሰ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
በዚህም በዞኑ ሁለት ወረዳዎች በተለይም አርሶ አደሩን በግፍ በመግደልና በመዝረፍ የጭካኔ ጥግ በማሳየት ላይ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ሸኔ የፖለቲካ ዓላማ የሌለው፣ በሌብነት እና ዝርፊያ ላይ የተሰማራ የህዝብ ጠላት መሆኑን በግልጽ አረጋግጧል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷ ቡድኑ ከዝርፊያ ባለፈ አርሶ አደሮችን በማገት፣ በማሰቃየትና በመግደል ብዙ ግፍና መከራዎችን እያደረሰ ነው፡፡
ስለሆነም ይህን አሸባሪ ቡድን ማጥፋት የሚቻለው በሕዝቡ የተባበረ ክንድ በመሆኑ የጋራ ጠላታችንን በጋራ መዋጋት አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ስር ባሉ በተለይም አመያ እና ወንጪ ወረዳዎች የአርሶ አደሩን ንብረት በመዝረፍ፣ ማውደም እና ሰዎችን በመግደል ጭምር ሽብር እየፈጠረ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በዞኑ የሚገኙ የጸጥታ አካላት በቅንጅት በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸው÷ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት በማጋለጥና በመዋጋት ጭምር ህዝቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡