Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጣሊያን የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ማሪና ሴሬኒ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
አቶ ደመቀ የጣሊያን መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ላደረገው ያልተቋረጠ የልማት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘውን ሳሊኒ ኢምፕሬጊሎ በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን የላቁ የግንባታ ስራዎችንም አድንቀዋል።
መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለማስቆምና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ አዎንታዊ እርምጃዎችን አብራርተዋል።
በተያያዘም የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሉ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ መደረጉን፣ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉ እና ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋምን በአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት በትግራይ ተፈፅመዋል ያሏቸውን ወንጀሎች በተመለከተ ባቀረቡት የጋራ ምርመራ ምክረ ሀሳብ መሰረት እርምጃ ለመውሰድ የፌደራል መንግስት ቁርጠኝነትን በማሳየት ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ጽኑ አቋም አጽንኦት ሰጥተው አብራርተውላቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የመንግስታቱ ድርጅት እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት በአማራ እና አፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት በተፈፀሙት ግፍና በደሎች ላይ ተመሳሳይ ምርመራ እንዲያደርጉ ይፈልጋል ብለዋል።
ከመንግስት ኃላፊነት እና ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ጋር ተያይዞ ለትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ አገልግሎት ለመስጠት የተደረገውን ጥረትም ገልጸውላቸዋል፡፡
መንግስት የወሰደው አበረታች እርምጃ ቢሆንም፥ በሽብር ቡድኑ በህወሓት በኩል በጎ ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለና ተንኳሽ ድርጊቱን እንደቀጠለ ገልጸው ፥ በቅርቡ በአፋር ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ጠቅሰዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሰላም ጥረቱን ወደ ጎን በመተው በአጎራባች ክልሎች ላይ እየወሰደ ያለውን
 ኢሰብዓዊ ድርጊት ለመቀጠል ታጣቂዎችን እየመለመለ እና እያሰለጠነ ነው ብለዋል።
ጣሊያንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪውን ሀሰተኛ ትርክቶችን ማመን እንደሌለበት አንስተው ፥ ቡድኑ ብዙ ጊዜ ፀረ-ሰላም ባህሪውን በሀሰተኛ ተግባሩ ለመደበቅ እንደሚጠቀምበትም አስረድተዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትሯ  የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን አበረታች ጥረት መንግስታቸው እንደሚያደንቅ ተናግረዋል።
ማሪና ሴሬኒ አክለውም ፥ ጣሊያን የቀጣናው መልህቅ ከሆነችው ከኢትዮጵያ ጋር የልማት አጋርነቷን እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማስፋት ትፈልጋለችም ነው ያሉት።
በሁለቱም በኩል የተደረገው ውይይት በጋራ መግባባት የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ በቀጣይ የሲሚንቶ ገበያ ትስስር ለመፍጠርም ቃል ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.