አድዋ የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ ነዉ- አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አድዋ የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ ነዉ ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡
አፈ-ጉባኤው 126ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን÷ በመልዕክታቸው በአድዋ የነበረው ጦር ኅብረብሔራዊ ጦር ነበር፣ በአብዛኛው ተመሳሳይ ቋንቋ የማይናገር ሁኖ ከሁሉም በላይ ሁሉን በሚያካትተው ኢትዮጵያዊ መለያ ባላቸው ከፍ ያለ ጽኑ እምነት በጋራ የተሳሰሩ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
በመልዕክታቸውም በደም በተነከረ መስዋዕትነት ጭቆናን ትቢያ አልብሰው ነጻነትን ያበሰሩ ውድ የሀገር ልጆች መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡
አፈ-ጉባኤው ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በደም በተነከረ መስዋዕትነት ጭቆናን ትቢያ አልብሰው ነጻነትን ያበሰሩ ውድ የሀገር ልጆች ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት እውነትን ይዛ ግፈኞችን የተፋለመችበት ጦርነት ነበር፡፡
አድዋ የሀገሩን ዜጋም ሆነ መላው የጥቁር የነጻነት ታጋዮች አንገታቸውን ቀና ብለው እንዲሄዱ ያስቻለ ድል ነው፡፡
በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዝናን ከሰጡ ድርጊቶችን አንዱ ነው፡፡
የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ፣ አንድ ትልቅ ድርጊት እንደመሆኑ ሁሉ የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረውን ያህል የተገዢዎችን አንገት ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ድል ምክንያትም የፖለቲካ መሪዎችም ሆነ ሌሎች አካላት አቋማቸውን እንደገና እንዲመረምሩ አስገድዷቸው ነበር፡፡
ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል (የአድዋ ድል) በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡
የአድዋ ድል ፋሽስቶችን ያስደነበረ፣ የነጻነት ታጋዮችን ይበልጥ ያጀገነ፣ በጭቆና የተደቆሱትን ዓይን የገለጠ ጦርነት ነው፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች በአድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ…ብለው ፃፉ፡፡
በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክን ለየአፍሪካና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተሞገሱ።
በዚህች ዓለም ላይ ከተደረጉ አብዛኞቹ ጦርነቶች ድል ያደረጉት የወታደራዊ መረጃ ብልጫ የነበራቸውና ፍትሕና እውነትን ፖለቲካዊ መሠረት ያደረጉት ናቸው፡፡
እኛ ሁለቱንም ነበረን፤ ዓላማችን የአገራችንን ጥቅምና ክብር ህልውናና ልዕልና ማስከበር ነፃነታችንን ማስጠበቅ ሲሆን፡- ይህም የፍትሕና የእውነት ነፍሥ ነው፡፡ በአገር ወዳዱ ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት አማካይነት ደግሞ በአውሮፓ ላይ የወታደራዊ መረጃ ብልጫን ተቀዳጀን፡፡ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ከውጪ ወራሪዎች ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ እውነትና ፍትሕን መሠረት አድርጋለች፡፡
የአድዋ ጦርነት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አሸናፊነትን ያበሰረ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲያዊ ረገድም ያስገኘው ድል ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ እንድትመደብ አድርጓታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በጠላት ወረራ ጊዜ ከውስጣዊ ችግራቸው ይልቅ የጋራ ጠላትን መመከትና የአገርን ሉዓላዊነት ማስከበር ላይ ለድርድር እንደማይቀመጡ ያሳያል፡፡
በአንድነት ጠላትን የገጠሙትም በመካከላቸው ልዩነትና መቃቃር ስላልነበረ ሳይሆን በጋራና በአገር ጉዳይ ላይ የሚለያዩ ባለመሆናቸው እንደነበርም ያሳያል፡፡ የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ ያላትን ሕብረብሔራዊነት ያሳየችበት ነው፡፡
የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መመስረት መሠረት የሆነ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የይቻላል መንፈስ እንዲጋባባቸው ያደረገ ታላቅ ታሪካዊ ድል ነው፡፡
ድሉ የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትሕ መሠረት ነው፡፡
እንኳን ለ126ኛ ጊዜ ለሚከበረው የአድዋ በዓል አደረሳችሁ!
የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ
አገኘሁ ተሻገር
የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ