የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እና የጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ማህጸን ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ግርማ፤ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምሰሶ፤የማይደበዝዝ በደምና በአጥንት የተፃፈ ደማቅ ታሪክ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ 126 ኛው የዓድዋ ድል በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል ከግዙፉ ተራራ በላይ ግዙፍ ሃአርና ህዝብ እንዳለ ለዓለም ያስተማረ የፓን አፍሪካኒዝም እና የጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ማህጸን ነው፤ ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅርታ ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው ብለዋል::
ከንቲባዋ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ዓድዋ፤የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ግርማ፤ የኢትዮጵያዉያን የአንድነት ምሰሶ፤ የማይደበዝዝ በደምና በአጥንት የተፃፈ ደማቅ ታሪክ !
እንኳን ለ126 ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
የዘንድሮ የዓድዋ ድል በአል ዳግም ዓድዋ በሚሰኙ ኢትዮጵያችንን ከመበተን የታደገ ፤ ዓባይን የብርሃን ጮራ እንዲያመነጭ ያደረገና እንዲሁም ዘርፈ ብዙ በአንድነት ክንዳችን የተገኙ ድሎች ታጅቦና ደምቆ የሚከበር በመሆኑ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ከመቼውም ጊዜ የተለየ ያደርገዋል፡፡
የዓድዋ ጀግኖች በርግጥም በሞታቸው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ፤ ነጻነትን ከነክብሩ አድምቀው የጻፉ ሞትን በነፃነት ድል የነሱ፤ ከአገር በላይ ምንም አለመኖሩን በግብር ያረጋገጡ ሰብዓ ግዙፋን ፤ ናቸው፡፡ ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በተግባር ኢትዮጵያን ሆነው፤ ኢትዮጵያን አክለው መዋደቃቸው፤ ዛሬ እኛን ከአንገታችን ቀና አድርጎናል፡፡ በኩራትና በሞገስ የምንራመድ ፤የስነ-ልቦና ከፍታን የተላበስን ህዝቦች አድርገዋታል፡፡
በአትዮጵያችን ፋና ወጊነት የዓለም ጥቁር ህዝቦችም ስለነፃነት ታሪክን መፃፍ ጀመሩ፡፡ ዓድዋ ይሄንን ደማቅ ታሪክ በክብር የቀደሰ ክቡር በዓላችን ነው፡፡ የዓድዋ ድል ከግዙፉ ተራራ በላይ ግዙፍ ሃገርና ህዝብ እንዳለ ለአለም ያስተማረ የፓን አፍሪካኒዝም እና የጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ማህጸን ነው፡፡ ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅር ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው::
ዓድዋ በኢትዮጵያም በአለምም ብዙ አድዋዎችን ወልዷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የውጪ ወራሪዎች በምንም ሁኔታና አቅም ቢመጡ አንገት ማስደፋትና መመለስ የሚችሉ ጀግና ህዝቦች መሆናቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ዛሬ ስለ ዓድዋ ስንናገር ስለበርካታ አድዋዎች ስንቅ ለመሰነቅም ጭምር ነው፡፡ ዓድዋን የምንተርክ ብቻም ሳንሆን ዓድዋን ኢትዮጵያን ለማበልፀገሰ ግዙፍ ሃሳብና ትልም የምናሳካበት መሆኑን በሚገባ እናውቃለን!!
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ ሳይቀር የሚያከፋፍል አጀንዳን ለመፍጠርና ልዩነትን የሚያጎሉትን ትተን እንደ አባቶቻችን ተልቀን፤ ኢትዮጵያን አክለን በአንድነት እንድናከብር ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያን ፣ ለአፍሪካም ሆነ የመላ ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ለሆናችሁ ለአድዋ ጀግኖች ይሁን፡፡ መልካም የዓድዋ ድል በዓል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!