Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎና ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አርማ ነው- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋደሎ ምልክትና ውጤት ነው ሲል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ፡፡
 
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 126ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
 
የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎና ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አርማ ነው!
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋደሎ ምልክትና ውጤት ነው፡፡
ለጦርነቱ መነሻ የሆነው በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የውጫሌ ውል ስምምነት አንቀፅ አስራ ሰባት የጣልያንኛውና የአማርኛው ትርጉም የተለየ ሃሳብ መያዙ ነው፡፡ የአማርኛው ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ልዕልና የሚያከብር ሲሆን የጣልያንኛው ትርጉም ግን የአገራችንን ሉዓላዊነት መደፈር ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል፡፡
 
ይህን የተገነዘበው የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ጥቅም በማይነካና ሉአላዊነቷን በሚያከብር መልኩ እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ውጤት ሳይመጣ ስለቀረ ወደ ጦርነት መግባት የግድ ሆነ፡፡
 
በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ አርበኞች በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ፋሽስታዊ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ወራሪ በአንድ ቀን ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ድል አድርገውታል፡፡
 
በዚህም ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በወታደራዊ መረጃ፣ በደፕሎማሲና በፖለቲካል ጥበብ የሰለጠነውን እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የፋሽስት ወራሪ ሰራዊት ዕቅድ በማምከን አድዋ ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጅታለች፡፡
 
የዓድዋ ድል በአፍሪካ የጦርነት ታሪክ ውስጥ የተከበረና የተደነቀ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ብስራት ነው፡፡ በአድዋ ጦር አምባ ታሪክ ለአገራቸው ነፃነትና ከብር ህይወታቸውን ለመስጠት ያልሳሱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአፍሪካ ምድር የነፃነትን ምስጢር በክቡር ደማቸው በአድዋ ተራሮች ላይ ፅፈው አልፈዋል፡፡
 
በፈሰሰው ክቡር የኢትዮጵያውያን ጀግኖች ደም ሰንደቅ ዓላማችን በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ደምቆና ከፍ ብሎ እንደተውለበለበ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ተጋድሎና ቆራጥነት በዓለም የነፃነት ምድር የጥቁር ህዝቦች አይበገሬነት ተምሳሌት ሆናለች፡፡
 
የዓድዋ ድል የአባቶቻችንን ጀግንነትና ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት ድል ሲሆን አገራችንን ከአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ በመታደግ በዓለም አቀፍ መድረክ ታዋቂነትን እንድታገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡
 
ድሉ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መመስረትንና በቅኝ ግዛት ለወደቁ አፍሪካውያን ነጻ መውጣት ታላቅ አስትዋጽኦ አበርክቷል፡፡
 
በጥቅሉ የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የኩራትና የክብር ምንጭ የሆነ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈ፣ የጥቁር ሀዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ወኔ በመሆን መነቃቃት የፈጠረና በአባቶቻችን ደም የደመቀ ታላቅ አንፀባራቂ ድል ነው፡፡
 
በመሆኑም የዘንድሮውን የዓድዋ የድል በዓል የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለ126ኛ ጊዜ በድምቀት ስናከብር በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የፈጠረውን አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍና የአባቶቻችንን አደራ አንግበን ሉዓላዊነታችንን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጽናት ላይ ማተኮር ይኖርብናል፡፡
 
በተለይ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እያደረሱብን ያለውን ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቋቋምና የትግራይ ወራሪ ኃይሎች በክልላችን በከፈቱት ጦርነት የደረሰውን ጉዳት በመልሶ ግንባታው እንቅስቃሴ ከመንግሥታችን ጎን በመቆም ሁለተናዊ እንቅስቃሴ ውሰጥ በንቃት መሰለፍ ይጠበቅብናል፡፡
 
ሀገራችን በሰላም በልማትና በዴሞከራሲ ሰርዓት ግንባታ የጀመረችውን ጉዞም በማስቀጠል የአድዋን ድል እጥፍ ድረብ ልናደርገው ይገባል፡፡
 
የዓድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን ኢትዮጵያዊ አንድነትና እሴት መልሶ በጽኑ መሰረት ላይ ለመትከል ቃል እየገባን መሆን አለበት።
 
እንኳን ለ126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
 
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
 
የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም.
ባሕር ዳር – ኢትዮጵያ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.