የሀገር ውስጥ ዜና

126ኛው የዓድዋ የድል በዓል በመላ ኢትዮጵያ ተከበረ

By Mekoya Hailemariam

March 02, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 126ኛው የዓድዋ የድል በዓል በመላ ኢትዮጵያ ተከበረ ።

በዓሉ በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።

በተመሳሳይ የኢፌደሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በተገኙበት በዓድዋ ድልድይ በድምቀት ተከብሯል።

እናትና አባት አርበኞች፣ ታዳጋዎች እና ወጣቶች ዓድዋን የሚዘክሩ የተለያዩ ትዕይንቶችን አቅርበዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትን እና በርካታ እንግዶች ታድመዋል።

126ኛውን የዐድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትናንት ባስተላፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ የዐድዋ ድል ኢትዮጵያን መንካት የሚያስከትለው መዘዝ ምን እንደሆነ አስተምሮ ያለፈ ደማቅ ሐውልት ነው ብለዋል።

ድህነትን፣ ኋላ ቀርነትንና መከፋፈልን፥ እነዚህ ሦስቱ ጠላቶቻችንን ካሽነፍን፣ ኢትዮጵያ በቀድሞ ጀግኖቿ የምትኮራ ብቻ ሳትሆን፣ በአዲሶቹ ጀግኖቿም በክብር የምትጠራ ሀገር ትሆናለች ነው ያሉት ።

ዐድዋና ኋላ ቀርነት፤ ዐድዋና ድህነት፤ ዐድዋና የእርስ በእርስ መከፋፈል አብረው እንደማይሄዱ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡ የዐድዋ ድል በዓልን፣ በበለጸገችው ኢትዮጵያ ዐደባባዮች፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጸንተን እንድናከብረው የመቁረጫው ጊዜ አሁን ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በየአብቃል ፋሲል

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!