Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድል በቀደመው፣ በአሁኑ እና በሚቀጥለው ዘመን በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለ126ኛው የአድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

አቶ ደመቀ በመልዕክታቸውም ፥ በረጅሙ የታሪክ ጉዞ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተው ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን መዳፈራቸው በግልፅ ይታወቃል ብለዋል።

በዘመን ሰንሰለት ሃገራችን በውስጥ እና በውጭ ጠላቶች የተቃጡባትን የጦርነት ጥቃት ተከትሎ፤ ድፍረትን በሚጠየፉ ጀግና ልጆቿ ፈታኝ አውዶች በድል እየተሻገረች እነሆ በክብር ዘልቃለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፥ ኢትዮጵያ በክብር የመዝለቋ አመክንዮ በዜጎቿ አንድነት እና ህብረት ጥንካሬ ላይ እንደተመሰረተ አያሌ ቱባ የታሪክ አብነቶችን ለማሳያነት በኩራት መምዘዝ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በትውልድ ቅብብሎሽ ከተመዘገቡት ቱባ የታሪክ አብነቶች መካከል የአድዋ ድል በዓል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታላቅ ማሳያ ሲሆን ፥ በቀደመው፣ በአሁኑ እና በሚቀጥለው ዘመን በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነውም ብለዋል።

የአድዋ ድል በዓል . . . ትናንትን በፅናት፤ ዛሬን በወኔ እንዲሁም ነገን በቁርጠኝነት የሃገራችን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ሳይሸራረፍ በክብር እንድትዘልቅ በትውልድ ልቦና የድል አድራጊነት መንፈስ የሚያጋባ የወል እሴታችን ነው ሲሉም ይገልጹታል አቶ ደመቀ በመልዕክታቸው።

የአድዋ ድል በዓል . . . የሃገር ልዑዓላዊነት እና ነፃነት የማስከበር ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ፤ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት መከበር ለፈጠረው ንቅናቄ የድል አድራጊነት ውሃልክ ያሰመረ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር እንደሆነም አንስተዋል።

በእኛ ዘመን እና ትውልድ ሃገራችን ልዑዓላዊነቷን ከሚዳፈሩ እና ነፃነቷን ከሚፈታተኑ ሃይሎች የተቃጡ መልከ-ብዙ ጥቃቶችን በጋራ በመመከት አንድነቷን ጠብቃ ጉዞዋን ወደፊት ቀጥላለችም ነው ያሉት።

በዘመናችን ሃገራችን የገጠሟትን ከባድ እና ውስብስብ ጥቃቶችን መመከት የተቻለበት ምስጢር ከቀደሙ አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ለአሸናፊነት ያበቃቸውን ወኔ በመውረስ እንዲሁም አንድነታችንን አጥብቀን እና ጠብቀን መጓዝ በመቻላችን ነውም ሲሉ አክለዋል።

አሁንም ቢሆን በሃገር ልዑዓላዊነት እና ነፃነት ዙሪያ የሚቃጡብንን ጥቃቶች በፅኑ አንድነት እየመከትን፤ በዕድገት ጉዞ ከፊትለፊት የሚጠብቁንን ውስብስብ ፈተናዎች እንድንሻገር ህብረታዊ የድል ልምምዳችንን በተግባር እንድናረጋግጥ አደራ ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም የአድዋ ድል በዓል መመኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስፍረዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.