126ኛው የዐድዋ ድል በዓል በተለያዩ ከተሞች ተከበረ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 126ኛው የዐድዋ ድል በዓል ድሉን በሚያስታውሱ ትዕይንቶች በተለያዩ ከተሞች ተከበረ።
በጎንደር ከተማ እየተከበረ የሚገኘው የዐድዋ የድል በዓል ጀግኖች አርበኞች ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ወጣቶች በነቂስ በመውጣት ድሉን ዘክረውታል።
የድል በዓሉን የማሰብ መርሃ ግብሩ ከሰዓት በኋላ ዝክረ ዐድዋ በተሰኘ የኪነ ጥበብ ክዋኔ እንደሚቀጥል ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
በተጨማሪም የ126ኛው የዐድዋ ድል በዓል በደብረማርቆስ ከተማ በድምቀት ተከበረ፡፡
የድል በዓሉ በከተማዋ በንጉስ ተክለ ሀይማኖት አደባባይ የዞንና የከተማ አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ ወጣቶች፣ አባት አርበኞች በተገኙበት በደመቀ መልኩ አክብረውታል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው ፥ ዐድዋ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጎህ የፈነጠቀበት የአፍሪካን ሰማይ በብርሀን ጸዳል ያፈካ የመላው ዓለም ጥቁር ማህበረሰብ የይቻላል መንፈሰን የዘከረ የትውልዶች ሁሉ እኩልነትን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የዞኑ ወጣቶች ልክ እንደ አባቶች በአንድነት የጀግንነት ወኔ አዲስ ታሪክን በመዘከር የማይፋቅ ታሪክን ማስረከብ እንደሚኖርባቸውን አመላክተዋል።
የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ፋንታነሽ አባተ፥ የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነው የዐድዋ ድል ወጣቱ የአባቶችን ታሪክ በመድገም ኢትዮጵያ የዓለም የነጻነት ተምሳሌትነትን ማስቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአምባሰል ወረዳ የጦርነቱ መነሻ በሆነው የውጫሌ ውል በተፈረመበት በይስማ ንጉስ ተከብሯል።
በዓሉ ተማሪዎችና መምህራን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ወጣቶች በተገኙበት መከበሩን ከአምባሰል ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክብረወሰን ኑሩ እና ሰላማዊት ሙሉነህ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!