የዓድዋ ድል በዓል በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት ተከበረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓድዋ ድል በዓል በቻይና ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና በቻይና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር በዌብናር አክብሮ ውሏል።
በበዓሉ በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ኢትዮጵያን ለዚህ ታላቅ ድል ያበቃት መላው ኢትዮጵያዊ ጾታ፣ ብሄርና ሃይማኖት ሳይለየው ሆ ብሎ በአንድነት ከጫፍ ጫፍ ተነስቶ በመዝመቱ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንደመስፈንጠሪያና ትልቅ ማነቃቂያ ሆኖ ያገለገለና ከኢትዮጵያውያን አልፎ በመላው አለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች በተለይም ለአፍሪካዊያን ኩራትን ያጎናፀፈ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ በንግግራቸው የዓድዋ ድል በአንድነት ቆመን ጠላትን ማሸነፍ እንደምንችል የተማርንበት ነው ያሉ ሲሆን፥ አሁን የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በበለጠ አንድነታችንን በማጠናከር ከፋፋይ የፖለቲካና የዘረኝነት አስተሳሰቦችን ድል የምናደርግበት ጊዜ መሆኑን ገለጸዋል፡፡
የዚህ ትውልድ ግዴታና አደራ አባቶቻችን፣ አያትና ቅድመ አያቶቻችን በየአውደ ውጊያው መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩልንን አገር መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ብልጽግና ማማ ማድረስም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በቻይና የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ተወካይ የሆኑት አቶ አስቻለው በላይ በበኩላቸው፥ በርካታ የሚያለያዩን ጉዳዮች ቢኖሩም ልክ እንደ ዓድዋው ሀገራዊ አጀንዳ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከምንግዜውም በላይ በመግባባትና በመደማመጥ አንድ ሆነን ችግሮቻችንን ልንቀርፍ ይገባል ብለዋል።
በቻይና የኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ተወካይ የሆኑት አቶ ሰላሙ ይስሐቅም፥ አባቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር፣ ታሪክ እና ክብር ጠብቀን፤ ከሃይማኖትና ጎሳ ንትርክ ወጥተን ለሁሉም የምትበቃ ምቹ ሀገር በመፍጠር ለተተኪው ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል ማለታቸውን ኤምባሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባከው መግለጫ አመልክቷል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!