የሀገር ውስጥ ዜና

የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ የቡና ማሠልጠኛ ማዕከልን ጎበኙ

By Alemayehu Geremew

March 02, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያና ሴሬቲ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ የቡና ማሠልጠኛ ማዕከል ጎበኘ፡፡

በጉብኝት መርሃ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላን ጨምሮ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት የተገኙ እንግዶች ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ግቢ ውስጥ የተገነባው የቡናውን ዘርፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬዳል ተብሎ የታመነበት ማሠልጠኛ ማዕከል በኢጣሊያ መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ድጋፍ የተሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ÷ የማዕከሉ ግንባታ በጥምረት የምናካሂደውን የልማት ትብብር ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ÷ ማዕከሉ በምስራቅ አፍሪካ በዘርፉ የመጀመሪያው ዘመናዊ ማሠልጠኛ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ላይ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በማሰልጠን እና በማብቃት የቡናውን ዘርፍ እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በቡና ምርምር ዘርፍ ላይ ከሚሠሩ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመላክታል።