Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ዙሪያ በጂንካ ከተማ እየመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከደቡብ ክልል የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ዙሪያ በጂንካ ከተማ ምክክር እያካሄዱ ነው፡፡

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ከደቡብ ክልል ከሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ የትምህርት ዘርፍ አካላት ጋር ነው እየመከሩ የሚገኙት፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ፥ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የገዘፈውን የጥራት መጓደል ለመፍታት ይሰራል።

በኢትዮጵያ ለትምህርት ተደራሽነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለጥራቱ ያለመጨነቅ ፣ የትምህርት ዘርፉ ከፖለቲካ ጋር መደበላለቅ፣ ትምህርት እና ብሔርተኝነት፣ የግብረገብነት ችግር እና ሌሎች ምክንያቶች ለትምህርት ዘርፉ የጥራት ማነስ መንስዔ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲዎቻችን እየተሰጠ ያለው ትምህርት የተማሪዎችን ብቃት የሚመዘንበት አይደለም ሲሉም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ተናግረዋል ።

በቀጣይ የመምህራንን አቅም ማሳደግ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም ትምህርትን ከፖለቲካ ነጻ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ፥ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባደረገው ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች 1ሺ85 ትምህርት ቤቶች ማፍረሱን ጠቁመዋል።

በዚህም የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በደረጃ የመገንባት ስራ ይሰራል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ ከውይይቱ በተጨማሪ በክልሉ የተመረጡ ትምህርት ቤቶችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

በመርሀ ግብሩ የደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.