Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የኩባንያውን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ስራ አፈፃጸም በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ወይዘሪት ፍሬህይወት በመግለጫቸው ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ተቋሙ የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን የገለጹት ወይዘሪት ፍሬህይወት፥ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 56 በመቶው ከድምጽ አገልግሎት 29 በመቶው ደግሞ ከሞባይል ዳታ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 41 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላሩ ከአለም አቀፋ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን ነው ተናገሩት።

የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 44 ነጥብ 4 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን ፥ የደንበኞች ቁጥርም 10 በመቶ መጨመሩ ተመላክቷል።

በቤዛዊት ተፈሪ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.