በድሬዳዋ ባለፉት 6 ወራት በማክሮ ኢኮኖሚው የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል – ከንቲባ ከድር ጀዋር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ባለፉት 6 ወራት በማክሮ ኢኮኖሚው የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን እና ምጣኔ ሀብቱ በ2014 ዓ.ም 12 በመቶ እንደሚያድግ መገመቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጀዋር አስታውቀዋል።
12 በመቶ እንደሚያድግ መገመቱም ከ10 ዓመት በኋላ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው የተመዘገበ ትልቅ ዕድገት መሆኑን ነው ጨምረው የገለጹት፡፡
በኢኮኖሚው ውስጥ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 45 በመቶ እና ግብርናው 8 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው በዕቅድ ተይዞ በመሠራቱም÷ ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩት ስራዎች አበረታች ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡
በአስተዳደሩ በገጠርና ከተማ ስራ ፈላጊ ሆነው ከተመዘገቡ 16 ሺህ 187 ሰዎች መካከል ለ8ሺህ 629 ስራ አጦች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉምንም አብራርተዋል፡፡
በስድስት ወሩ 1 ቢሊየን 52 ሚሊየን 702 ሺህ 951 ነጥብ 65 መንግስታዊና ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን ለማመንጨት ታስቦ ከዕቅዱ በላይ 1 ቢሊየን 052 ሚሊየን 800 ሺህ 430 ነጥብ 74 ብር ማግኘት መቻሉ ተጠቁሟል።
አስተዳደሩ በካፒታል አፈፃፀም ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት 11 ፕሮጀክቶችን ያጠናቀቀ ሲሆን÷ 13 ፕሮጀክቶች ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙም ነው ከንቲባው ለምክር ቤቱ ያብራሩት፡፡
በተመሳሳይ በግብርናው ዘርፍ የመስኖ ልማት በአትክልትና ቡና በ2ሺህ 780 ሄክታር መሬት ሰብሎችን በመሸፈን ከ725 ሺህ በላይ ኩንታል ለማምረት ታቅዶ÷ 2 ሺህ 637 ሄክታር በመሸፈን 725 ሺህ 373 ኩንታል ማምረት ስለመቻሉም ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማን የአስፓልት መንገድ ግባን በተመለከተም ከ30 ኪ.ሜ በላይ የመንገድ ስራ በአስተዳደሩና በፌደራል መንግስት ትብብር እየተገነቡ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡
ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች አዲስ የውሃ መስመር በመዘርጋት የውሃ መስመር ማሻሻያ በማከናወን፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ጥገና በማካሄድና በጨው በተደፈኑ መስመሮች በመቀየር ውጤታማ ስራ በመስራት ባለፉት 6 ወራት 9 ሚሊየን ሜ.ኩ ውሃ ማምረት ሰለመቻሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጀዋር አስታውቀዋል።
በእዮናዳብ አንዱዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!