ከ31 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በሐሰተኛ ሰነድ ወደ መሃል ሀገር ሊገባ የነበረ ግምታዊ ዋጋው ከ31 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ መያዙን በጉምሩክ ኮሚሽን የአዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-62657-ኢትና የተሳቢ ቁጥር 18099 የሆነው ከባድ የጭነት ተሸከርካሪ በሁለት ኮንቴነሮች የጫነውን የኮንትሮባንድ ዕቃ ጨለማን ተገን በማድረግ ለማሳለፍ ሲሞክር መያዙን በጽህፈት ቤቱ የኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ዓለሙ ይመር ተናግረዋል፡፡
ዕቃው መነሻውን ድሬዳዋ በማድረግ በሚሌ-ኮምቦልቻ መሥመር ህጋዊ በማስመሰል ከውጭ ወደ መሃል ሀገር ለማስገባት የተዘጋጀ እንደነበርም አስረድተዋል።
ለዚህም የተለያዩ ሐሰተኛ የጉምሩክ ሰነድና የኮንቴነር ማሸጊያ በመጠቀም እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የጉምሩክ ጣቢያዎችን ለማሳለፍ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ለጽህፈት ቤቱ የመረጃ ሠራተኞች በደረሰ ጥቆማ መሠረት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ልዩ ቦታው “ብርጌድ” በተባለው ሥፍራ የኮንትሮባንድ ዕቃውን መያዝ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ከ50 ሺህ ስቴካ በላይ ሲጋራና ከ3 ሺህ 700 ስቴካ በላይ ሺሻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ እንደሚገኙበት ኢንስፔክተር ዓለሙ ጠቅሰዋል።
የተሽከርካሪው ሾፌርና ረዳቱ በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ዕቃዎቹን ለማሳለፍ ተባባሪ በመሆን ከተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል አንድ የ”አርበረከቴ ” ፍተሻ ጣቢያ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና ሌላውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ቡድን መሪው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!