ሚኒስቴሮቹ በጥምረት ለመስራት የጀመሩት እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን እየሠሩ መሆናቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በጥምረት ለመሥራት የጀመሩት እንቅስቃሴ በውጤት እንዲታገዝ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ሁለቱ ሚኒስቴር መ/ቤቶች የቀጣይ ክህሎት ስልጠናና ቴክኖሎጂ ፍላጎት ማሳያ ጥናት ላይ ውይይት በማካሄድ በቀጣይ ወራት የሚፈፀሙ ዕቅዶችን ዛሬ አፅድቀዋል፡፡
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እና በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በተመራው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው÷ ሚኒስቴሮቹ በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በጥምረት ለመሥራት የጀመሩት እንቅስቃሴ በውጤት እንዲታገዝ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
በተለይም በዘርፉ የሚታዩ የማዘጋጃ ቤቶች አገልግሎቶችንና ሌሎች የከተማ አገልግሎት አሰጣጦችን ለማሻሻልና የሕዝብ እርካታ ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ወ/ሮ ጫልቱ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት በበኩላቸው÷ በሀገራችን ያለውን የሥራ ባህል ከመለወጥ በተጨማሪ አገር በቀል እውቀትን ለማሳደግና በእጃችን ያሉ የሥራ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም በጋራና በመናበብ ውጤትን መሰረት ባደረገ መልኩ መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በቀጣይ ወራት የሚከናወኑ ዕቅዶች ላይ ውይይት ተካሂዶ የፀደቀ ሲሆን፥ በጋራና በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ መሰጠቱንም ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡