Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ከሚያዚያ ወር አጋማሽ በኋላ እንደሚሻሻል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል የዘንድሮው የበልግ ዝናብ አገባቡ የተዳከመ ቢሆንም ከሚያዚያ ወር አጋማሽ በኋላ እየተሻሻለ እንደሚመጣ የሶማሌና የአጎራባች ክልሎች የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የሶማሌና የአጎራባች ክልሎች የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ ፣ ትንተናና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አስተበባሪ አቶ አሸናፊ ሙሉነህ የ2014 ዓመት የበጋና የበልግ የዝናብ ስርጭት ሁኔታን አስመልክተው በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ አሁን ያለው የበልግ ዝናብ ወቅት አጀማመሩ የተዳከመ ይሁን እንጂ ከመጪው ሚያዚያ ወር አጋማሽ በኋላ የዝናብ ስርጭቱ እየተሻሻለ እንደሚመጣ አብራርተዋል።

አስተባባሪው በመግለጫቸው፥ ያለፈው የበጋ የዝናብ ወቅትን ሊያዳክሙ የሚችሉ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ምክንያት አብዛኛው የበጋ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሰሜን የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የበጋ የዝናብ ስርጭት አነስተኛ እንደነበረ ጠቁመው ፥ ይህም በክልሉ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዚያና ግንቦት ወራትን በሚያካትተው የበልግ ዝናብ ወቅት ደቡባዊ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው መሆኑን የጠቀሙት አቶ አሸናፊ፥ የዘንድሮው የበልግ ዝናብ አጀማመር የተዳከመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮ የበልግ ዝናብ ወቅት በሰሜንና በደቡብ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች ከ25 እስከ 35 ከመቶ ከመደበኛ በታችና ከመደበኛ በላይ ሊሆን እንደሚችል መተንበዩን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በክልሉ ያለውን ድርቅና የዝናብ እጥረት በመገንዘብ ዝናብ መጣል ሲጀምር የዝናብ ውሃን በአግባቡ ማጠራቀምና መጠቀም እንዳለባቸው አስተባባሪው ማሳሰባቸውን ከሶማሌ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.