ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍ ያለ ፍላጎት አላት – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ አዲስ የተመደቡትን የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸው ፥ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳላት ገልጸውላቸዋል።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን እና ኮሚሽነሮችም መሾማቸውን ጠቅሰው÷ በቅርቡም ሀሉን አቀፍ ምክክር እንደሚጀመር ገልፀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከእስር መፈታት እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት መንግስት ለዘላቂ ሰላም መስፈን የወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች መሆናቸውንም አንስተዋል።
አክለውም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ የሰብአዊ መብት ተቋም በጋራ ባካሄዱት የምርመራ ውጤት የሰጧቸውን ምክረ ሀሳቦች መንግስት አየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም የህወሓት የሽብር ቡድ በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸመውን በርካታ የግፍ ተግባራት በተመለከተ ተገቢው ምርመራ መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል መንግስት በትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጉን ገልፀው፤ የህወሃት ቡድን ግን በአፋር ክልል ዳግም ግጭት በመቀስቀሱ የሰብዓዊ አቅርቦቱ መስተጓጎል እንደገጠመው ጠቅሰዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም የህወሓት የሽብር ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች ለሚያደርገው የጸብ አጫሪነት ድርጊቱ አሜሪካ ተጠያቂ ታደርገዋለች ብላ ኢትዮጵያ ትጠብቃለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን ከአግዋ የቀረጥ ነጻ እድል የማስወጣት እርምጃ አንዲሁም የHR 6600 ረቂቅ ህግ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ጊዜ ግንኙነት የሚመጥን አለመሆኑንም አቶ ደመቀ በአንጽንኦት አስረድተዋል።
አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን በበኩላቸው፥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ላደረጉቸው ገለጻ አመስግነው፥ ሀገራቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሰብዓዊ ጉዳዮች የሚያሳስባት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከሮ እንደሚሰሩም ነው አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ያስታወቁት።
በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ ስራ እንዲያከናውኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡