ሀገራዊ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርን ከፊት ማስቀደም አለባቸው – የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ ያሳካ ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርን ከፊት ያስቀደመ አካሄድን መከተል እንደሚጠበቅባቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም እና የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ሊቀመንበር አባገዳ ሮበሌ ታደሰ ፥ ምክክሩ ዜጎች የሚፈልጓትን ሀገር እዉን ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስክነት እና ቅንነት በተሞላበት መንገድ መንቀሳቀስ አለብን ነው ያሉት፡፡
ፍሬያማ ምክክሮች ይደረጉ ዘንድ የፓለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃኑ ከጥቃቅን ሃሳቦች ወጥተው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ መሀመድ አበጋዝ በበኩላቸዉ፥ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታዉ ከሀገር ተሻግሮ እንደ አህጉር ለኢትዮጽያ ከሚሰጠዉ ጥቅም አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ፥ ፓርቲዎች ከአባላትና ደጋፊዎቻቸዉ ጋር ለሀገራዊ ምክክሩ ዉጤታማነት በጋራ መሥራት ይገባቸዋል፡፡
በፖለቲካዉ መስክ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ባሻገር ሌሎች ባለድርሻዎችም በተመሳሳይ ሀገራዊ ኃላፊነታቸዉን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የፓርቲ ኃላፊዎቹ አጽንኦት የሰጡት፡፡
በአወል አበራ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!