ጠ/ሚ ዐቢይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በማረፋቸው የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በማረፋቸው ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማቸው ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህብራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባወጡት መግለጫ፥ ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው ወሳኙን ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።
ነገሮችን በአርምሞ እየተመለከቱ ሀገራችንን በጸሎት ያግዙ እንደነበርም ነው ያመለከቱት።
በዚህ ወቅት እርሳቸውን ማጣት ከባድ ጉዳት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ለሁላችንም መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።