የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አራተኛ ፖትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕረፍት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለህዝበ ክርስቲያኑም መፅናናትን ተመኝቷል።
አቡነ መርቆሬዎስ ህይወታቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰጡ የሃይማኖት አባት መሆናቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያምናልም ብሏል ምክር ቤቱ በሃዘን መግለጫው።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እረፍት የተሰማትን ሐዘን ገልጻለች፡፡
ቤተክርስቲያኗ ለመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም እህት ለሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሐዘናቸው ተካፋይ መሆኗንም ነው የገለጸችው።
በተያያዘም የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል÷ ቅዱስነታቸው ነገሮችን በጸሎት፣ በትዕግሥትና በአርምሞ እየመረመሩ ከባድ የሚመስሉ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ በማለፍ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀሱ አባት መሆናቸውን አስታውሷል፡፡
በቅዱስነታቸው ዕረፍት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለጸ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና ብፁዓን አባቶች መጽናናትን እንመኛለን ብሏል፡፡