Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በባሕር-አየር ሎጅስቲክስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የጂቡቲ አየር መንገዶች፣ የጅቡቲ ዓለምአቀፍ ነጻ ቀጠና እና ወደብ ባለስልጣን እንዲሁም የዶራሌ ደረቅ ጭነት ወደብ አገልግሎት በባህር – አየር ሎጅስቲክስ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ አምባሳደር መሐመድ ሀሰን እና የጅቡቲ ነፃ ቀጠና እና ወደብ ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦማር ሃዲ ተገኝተዋል።

በዘርፉ የተፈረመው የሁለቱ ሀገራት የአጋርነት ሥምምነት ቀጠናዊ ትሥሥሩን ይበልጥ በአየር ፣ በየብስ እና በባህር በማሳለጥ ያጠናክራል ተብሎለታል፡፡

በባህር – አየር የሚሠጠው የጭነት አገልግሎት በባህር ብቻ ከሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት በሁለት እጥፍ የተቀላጠፈ እና በአየር ከሚሰጠው የጭነት አገልግሎት አንጻርም ክፍያው በሁለት እጥፍ እንደሚያንስ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን ንግድ፣ ግብይት እና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት እና በማሳለጥ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የአሁኑ ስምምነትም የወደብ አገልግሎት እና ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የላቀ እመርታ እና ትርፍ እንዲኖር ያግዛል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ባለፈም የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና በቀጣይም ሀገራቱ ፖሊሲዎቻቸውን ከኢኮኖሚያቸው ጋር በማጣመር ለዕድገታቸው የሚሰሩበትን ምህዳር እንደሚፈጥር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የባህር-አየር ካርጎ አገልግሎትን ለመጀመር የዛሬ አመት የተስማሙ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም በይፋ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የሸቀጦችን ዝውውር በማቀላጠፍ የአህጉሪቱን ንግድ ይበልጥ ማሳለጥ እንደሚያስችል ሲታመን ሃገራቱም በአገልግሎቱ ላይ ባለፈው አነድ አመት ሲሰሩ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

የአገልግሎቱ መጀመር በተለይ ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚሻገረውን ምርትና ሸቀጥ በባህር-አየር የጭነት አገልግሎት በማያያዝ ከጂቡቲ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፈጣን የካርጎ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ታምኖበታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.