የካራማራው ድል ለሀገራቱ ወዳጅነት እና ወንድማማችነት ጽኑ መሠረት ሆኗል – የኩባ አምባሳደር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ጆርጅ ለፌበር ኒኮላስ በኦጋዴን ጦርነት 44ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ በኢትዮጵያውያን የካራማራው ጦርነት ድል እየተባለ ስለሚጠራው ታሪክ አውስተዋል፡፡
አምባሳደር ጆርጅ ለፌበር ኒኮላስ ÷ የኢትጵያ ወታደራዊ ኃይል ከኩባውያን ታጋይ አጋሮቻቸው ጋር በመዝመት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት ሊደፍር የመጣውን የሶማሊያ ኃይል አሸንፈዋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ የኩባ አብዮት ዋና አዛዥ የሆኑት ፊደል ካስትሮ ÷ ይህን ኩባ ለኢትዮጵያ ያደረገችውን ዓለምአቀፋዊ ወታደራዊ ድጋፍ “የባራጓ ኦፕሬሽን” ብለው ይጠሩት እንደነበርም አምባሳደሩ አውስተዋል፡፡
በዘመቻው 163 ኩባውያን ታጋዮች እንደተሰው ተመልክቷል፡፡
የኩባውያን ታጋዮች መስዋዕትነት ለሀገራቱ ወዳጅነት እና ወንድማማችነት ጽኑ መሠረት ሆኗልም ነው ያሉት አምባሳደሩ፡፡
የኩባና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከፈረንጆቹ 1970 ጀምሮም ከ 5 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም ከኩባ ዩኒቨርሲቲዎች እንደተመረቁ ነው የተመለከተው፡፡
የኩባ መንግስት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል መሥጠት መቀጠሉን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
በጤናው ዘርፍም ኩባ ሐኪሞችን በመላክ በአዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ የኩባ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
የካራማራ ድል 44ኛ ዓመት ነገ ታስቦ ይውላል፡፡