44ኛው የካራማራ የድል በዓል በኢትዮ- ኩባ አደባባይ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ምንም ልዩነት ሳይገድባቸው የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበት 44ኛው የካራ ማራ የድል በዓል በኢትዮ- ኩባ አደባባይ እየተከበረ ነው::
በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ በጦርነት የተሳተፉ የወቅቱ የሠራዊት አባላት ዐርበኞች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል::
የበዓሉን መርሃ ግብር÷ ኮረማሽ የጉዞ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ እና የኩባ ሕዝቦች ወዳጅነት ማኅበር፣ የህጻናት አምባ ልጆች ከአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝም እና ኪነጥበብ ቢሮ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ነው::
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ኪነጥበብ ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሀት÷ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው በከፈሉት የህይወትና አካል መስዕዋትነት ወረራውን ቀልብሰው ድል ያደረጉበት ደማቅ ስፍራ የሚይዝ ታሪካችን ነው ብለዋል::
በዓሉ ለቱሪዝም ዘርፋ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ ወደፊት በስፋት እንደሚሰራበትም ጠቁመዋል::
ካራ ማራ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችን በአንድነት የዚያድባሬን የወረራ ህልም ያከሸፋበትና ድልን የተቀዳጁበት፣ ዳግም ዐድዋን እውን ያደረጉበት በመሆኑ÷ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በመስራት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ ይኖርበታል ሲሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የበዓሉ ተሳታፊዎች ገልፀዋል::