Fana: At a Speed of Life!

ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ጋር በመሆን ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች ያለምን የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቁና የሀገራችን ገጽታ እንዲገነባ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ሰሞኑን በሀገራችን በታላቅ ድምቀት በተከበሩት የአድዋ ድል በዓልን እና በዛሬው ዕለት ተከብሮ በዋለው የካራማራ ድል በዓል ላይ በመገኘት በሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና በህዝብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረዋል።

ደከመን ሰለቸን ሳይሉ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ሌት ተቀን የሚጠብቁ የፀጥታ አካላትን ክብር አስፀያፊ ስድቦችን በመሳደብ ደፍረዋል።

ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ለመግባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።

ይሁን እንጂ የፀጥታ ኃይሎች ሁሉንም ትንኮሳዎች በትግስት በማለፍ በዓላቱ በሰላምና በድምቀት እንዲከበሩ አድርገዋል።

እነዚህ ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፈልጉትን ህግና ስርዓት ተከትለው ማድረግና ሐሳባቸውን በነፃና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተፈቀደላቸው ስፍራ ማራመድና መፈፀም ሲችሉ ብሄርን ከብሄር፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት ጋር ለማጋጨት ስራዬ ብለው ሌት ተቀን በህቡዕ እና በግልጽ ጭምር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ግብረ-ኃይሉ ደርሶበታል።

በመሆኑም እነዚህ ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ግብረ-ኃይሉ እያሳሰበ ማንም ከህግ በላይ ስላልሆነ ህግን ጥሰን ድርጊታችንን እንቀጥላለን የሚሉ ከሆነ የጋራ ግብረ ኃይሉ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድና በህግም ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ያሳስባል።

በመጨረሻም ሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ይህንን ተገንዝቦ ከተማውንና አካባቢውን ነቅቶ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር እንዲጠብቅ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ግብረኃይሉ ይጠይቃል።

የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም

ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.