ዶ/ር ሊያ በ4ኛው የዱባይ ጤና ፎረም ላይ በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ አካፈሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት በማሳደግ ዙሪያ የኢትዮጵያን ልምድ አካፈሉ፡፡
ሚኒስትሯ በዱባይ ጤና ጥበቃ ባለስልጣን በተዘጋጀው 4ኛው የዱባይ ጤና ፎረም ላይ በመሳተፍ ‘በጤና አጠባበቅ አቅርቦት ላይ ጥራትን እና ብቃትን ማሻሻል’ የኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ዋና መሰረት በማድረግ ጥራትን በማሳደግ ዙሪያ ልምድ ማካፈላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
ከዱባይ ጤና ባለስልጣን፣ ናባዳት ኢኒሼቲቭ፣ ኑር ዱባይ ፋውንዴሽን እና ቪፒኤስ ጤና ጥበቃ ጋር በልዩ ልዩ እና የመጀመሪያ ደረጃ ክብካቤ ዙሪያ ባሉ የትብብር ዘርፎች ላይ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማካሄዳቸውንም አንስተዋል።
ዶክተር ሊያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት እና የግል ተቋማት በኢትዮጵያ በተለያዩ የጤና ልማት ስራዎች ላይ ላደረጉት ትብብር እና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።