አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ የተራራ ላይ የብስክሌት ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የ16 ኪሎ ሜትር የተራራ ላይ የብስክሌት ውድድር ተካሄደ።
መነሻውን በወረዳው ፣ በመሃል ወንዝ ቀበሌ ባደረገው የብስክሌት ውድድር ከ60 በላይ ብስክሌተኞች ተሳትፈዋል ።
ከውድድሩ አዘጋጆች አንዱ የሆነው “የዳይናስቲክ ኢትዮጲያ አስጎብኚ ድርጅት” ሥራ አስኪያጅ ቦጋለ አባይ ÷ ውድድሩ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን የቱሪዝም መስክ በማነቃቃት በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ ከተካሄደው የተራራ ላይ የብስክሌት ውድድር በተጨማሪም የእግር ጉዞ እና የአየር ላይ ቀዘፋ መካሄዱንም ተመልክቷል።
በውድድሩ የሀገር ውስጥ ብስክሌት ጋላቢዎችና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሌሎች ሀገራት ቆንስላ ሠራተኞችም የተሳተፉ ሲሆን አስከ 300 ሺህ ብር ገቢ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።
ውድድሩ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከ”ተሥፋ ቱር”፣ “ዳይናስቲ ኢትዮጵያ ቱር”፣ “ሰሜን ኢኮ ቱር” እና ከሌሎች አጋር የጉዞ አስጎብኚዎች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡