ሚኒስቴሩ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበጀት አመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ዙሪያ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ መግለጫቸውእየተሰሩ ካሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ጎን ለጎን የህግ የበላይነት በማስከበር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በታማኝነት በወቅቱ ግብራቸውን ለሚከፍሉ ዜጎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በህገ ወጥ ድርጊት የተሳተፉ 166 ድርጅቶች መለየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ሀስተኛ ደርስኝ መሽጥ ለግብር አስባስቡ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከ166 ድርጅቶች መካከል 136 ያህሉ ከ 6ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ማድርጋቸውን በመረጃ ቋት ውስጥ መገኘቱን ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህም መካከል 16 ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከብሄራዊ መረጃ እና ደህነት እና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት የህግ ማስከበሩን ስራ እየተስራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
166 ድርጅቶች ምንም ዓይነት የሚሽጡት ዕቃም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት የሌላቸው ሲሆን በሀስተኛ መታውቂያ፣ በሀስተኛ አድራሻ ፈቃድ ሳይኖራቸው ደረሰኝ ያሳትሙ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 57 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማከናወኑንም አንስተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ በሀምሌ ወር 18 ቢሊየን ብር፣ በነሀሴ ወር 20 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እና በመስከረም ወር 19 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ነው የተናገሩት።
በ18 የገቢዎች ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም ከሀገር ውስጥ ገቢ 31 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ፣ ከውጪ የንግድ ቀረጥ እና ታክስ 24 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እና ከሎተሪ ሽያጭ 46 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች 21 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡንም አስረድተዋል።
በሲሳይ ጌትነት