ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና አንዳንድ የእንግሊዝ ፖለቲከኞች በታይዋን ጥያቄ ላይ “በእሳት ከመጫወት” እንዲታቀቡ አሳሰበች

By Alemayehu Geremew

March 07, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ አንዳንድ የእንግሊዝ ፖለቲከኞችን በታይዋን ጥያቄ ላይ “በእሳት ከመጫወት” እና ከጸረ-ቻይና ሤራቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ፡፡

በፈረንጆቹ መጋቢት ሦስት በዩናይትድ ኪንግደም “የታይዋንን ዴሞክራሲ እንደግፍ” የሚል የክርክር መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

በመድረኩ ታይዋንን “የሩቅ ምስራቋ ዩክሬን” ብለው በመፈረጃቸው ቻይናን እንዳስቆጣት ሲጂቲ ኤን አመልክቷል፡፡

በክርክር መድረኩ የዩናይትድ ኪንግደም ጸረ- ቻይና አቀንቃኞች ለታይዋን ድጋፍ እና ከለላ እንደሰጡና የዩናይትድ ኪንግደም መንግስትም እንደደገፈው ነው የተገለጸው፡፡

በሀገሪቱ የሚገኘው የቻይና ቃል-አቀባይ የታይዋንን ጥያቄ ከዩክሬን ጉዳይ ጋር ማወዳደር ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለውና ቻይና እንዲህ ያሉ አስነዋሪ አካሄዶችን አጥብቃ እንደምታወግዝ ነው ያስታወቁት፡፡

“የዩናትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች ታሪካችንን እና የቻይናን ወቅታዊ ሁኔታ አያውቁም ፤ የህዝባችንንም አንድነት ሳይረዱ ንቀውናል” ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡

ቃል-አቀባዩ ÷ ቻይና አንድ ሀገር እንደሆነችና ፣ ታይዋንም ከቻይና ተነጥላ የማትታይ የቻይና ክፍል እንደሆነች ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ አሳስበዋል፡፡

ቻይና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ከዓለም ሀገራት ጋር መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትሠራም ነው የተመለከተው፡፡