Fana: At a Speed of Life!

ጫት በሃገር አቀፍ ደረጃ እያስከተለ ባለው ጉዳት ዙሪያ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጫት መቃም በሃገር አቀፍ ደረጃ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በተመለከተ በቢሾፍቱ ከተማ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

አውደ ጥናቱን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የስርዓተ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከያ ዳይሬክቶሬት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።

በምክክር አውደ ጥናቱ ላይ ከ50 የሚበልጡ የጤናው ዘርፍ ተመራማሪዎች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የስራ ኃላፊዎች የፖሊሲ አውጭ አካላት ተሳትፈዋል።

እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የጤና ምርምር ተቋማት፣ የጤና ሙያ ማህበራትና አጋር ድርጅቶች እና በጫት ላይ ለበርካታ ዓመታት ጥናትና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ዓውደ ጥናቱ ጫት በኢኮኖሚ፣ በጤና እና በማህበራዊ ሁኔታዎች ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት የሚያሳዩ የምርምር ስራዎችና ውጤቶች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህ ባለፈም መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ በዘላቂነት ለሚሰራቸው ስራዎች  እንደግብዓት የሚያገለግሉ ሃሳቦችን እና መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ፥ ጫትን አስመልክቶ የተለያዩ ተመራማሪዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የምርምር ስራዎች መስራታቸውንና በዚህ ዙሪያ በጤና ሚኒስቴር እና በኢንስቲቲዩቱ ከፍተኛ አመራር አካላት በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

በአውደጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም ጫት በምስራቅ አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ በሰፊው እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ኢንስቲቲዩቱ ባካሄደው ስር የሰደዱ የማይተላለፉ በሽታዎች ስርጭትና መጠን የዳሰሳ ጥናት እንዳመላከተው፥ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 69 ዓመት ከሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 16 በመቶ የሚሆኑት ጫት ይቅማሉ።

ከእነዚህ መካከል 58 በመቶ ጫትን በየቀኑ የሚቅሙ ሲሆን፥ እየቃሙ የሚያጨሱት 16 በመቶ እንዲሁም ከቃሙ በኋላ አልኮል የሚጠጡት ደግሞ 32 በመቶ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.