በቦረና ዞን ከ14 ዓመታት በፊት የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እስካሁንም አልተጠናቀቀም
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ግንባታው በአምስት አመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ከ14 ዓመት በፊት የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እስካሁንም አልተጠናቀቀም፡፡
የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በፌደራል መንግስት 5 ቢሊየን ብር በጀት ሲጀመር 2 ሺህ ኪሎ-ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታን በአምስት ደረጃ የማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ነበር።
የግንባታው ፌዝ በቢሊኮ፣ በገልቸት፣ በጎብሶ፣ ተልተሌ እና ሳሪቴ በአምስት ዓመታት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥም ነበር የተጀመረው።
የግንባታ ሂደቱ ሳይሳካ በመቅረቱ ችግሩ ተፈቶ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ባለፈው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ለኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እንዲሰጥ መደረጉን የዞኑ የስራ ሃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
የቦረና ዞን ውሃ እና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋቆ ሊበን የፕሮጀክቱ ግንባታ ለሰውና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ፣ ለመኖ ምርት እንዲሁም የመስኖ ልማት ታሳቢ ተደርጎ ከ14 ዓመታት በፊት ግንባታው መጀመሩን ያስታውሳሉ።
በአካባቢው በሚከሰተው የውሃ እጦት ሳቢያ ወደ ጉረቤት አገራት የሚሰደዱ የዱር እንስሳትን ፍልሰት ለመታደግም ፕሮጀክቱ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ግንባታው መጀመሩን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ለውጥ ከመጣ በኋላ በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የነበረው ችግር እንዲፈታ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት ውሉ በድጋሚ ለኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መሰጠቱን አቶ ዋቆ ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ለሁለተኛ ጊዜ ውል በመውሰድ ወደ ስራ ከገባ አንድ ዓመት እንደሆነው አስታውሰው አሁንም የተለያዩ ነገሮች በሰበብነት እየተነሱ የበርካታ አርብቶ አደሮችን ችግር ሊፈታ ይችል የነበረው የውሃ ፕሮጀከት መቋጫ አላገኘም ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ክንውን አሁንም በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን ጠቅሰው ለዞኑ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ጉዳይ ባለፈው ዓመት ተነስቶ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ወስጥ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንደነበር አስታውሰው ሆኖም አፈጻጸሙ አሁን ላይ 37 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን አስድረተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ የአንድ ታዳጊ ወጣት ዕድሜ ቢያሥቆጥርም “ከተባለው ልማት ያገኘነው የውሃ ጠብታ የለም” ሲሉ በአካባቢው ተገኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተገናኘም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ እውን ሆኖ ቢሆን ይህ ሁሉ ችግር ባልደረሰብን ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የውሃ ፕሮጀክቱን በማከናወን ላይ የሚገኘው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ክፍሉ ለማ፥ የመጀመሪያው ውል በዲዛይን ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሰው አሁን ለሁለተኛ ዙር የገባውን ውል በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የወሰዱትን የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ በተባለለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ የነበረው የኮኔክተር ችግርም አሁን መፈታቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን እየሰሩ ያሉትን የውሃ መስመር ዝርጋታ በተባለው ጊዜ ቢያጠናቀቁም ፕሮጀክቱ እውን ሆኖ ግን ለህዝቡ አገልግሎት መስጠት እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ በፊት ተተክለው የነበሩ የኤሌክትሮ መካኒካል መሳሪያዎች የማይሰሩ በመሆናቸው በአዲስ መተካት ስላለበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!