ለሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ገለፁ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ገለፁ።
አባላቱ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬት፣ ዴሞክራሲያዊነት እና ፍትሃዊነት እንደ አንድ ዜጋ እንዲሁም እንደ ህዝብ ተወካይም ድርብ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይናገራሉ።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ያሉት የምርጫ ሂደቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ መመራት እና ሀላፊነት በተሞላበት አኳሃን መሄድ አለበት የሚሉት አባላቱ፥ ይህ ትልቅ የዴሞክራሲ ማሳያ በሁሉም አካላት ሊደገፍ ይገባዋል ይላሉ።
ከኢትዮጵያዊነት፣ ጨዋነት እና ሌሎች መገለጫዎች ያፈነገጡ ክስተቶች ሊታረሙ እንደሚገባም አንስተዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች የስልጣን በትርን ከመቆናጠጥ በላይ ለሀገር ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸውም ይገልጻሉ፤ ከራስ ፍላጎት ህዝብን ማድመጥ እንደሚቀድም በመጥቀስ።
ህዝቡም ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ከሚዛናዊነት እንዳያሸሸው በሰከነ አእምሮ ይበጀኛል የሚለውን ለመምረጥ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚኖርበትና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ ሁኔታ በራቸውን መክፈት አለባቸው ይላሉ።
በህግ እና ደንብ ያልተቃኘ የምርጫ ነጻነትን እና ራስን በራስ የማስተዳደር የዴሞክራሲ ጮራን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ህዝቡና ፖለቲከኞች ለዚህ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
አባላቱ አያይዘውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ስክነትን ባስቀደመ መልኩ ሀገርን በሚያሻግር እሳቤ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በአፈወርቅ አለሙ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision