የልማት ተነሺ ባልሆኑ ሰዎች ስም ከ65 ሚሊየን ብር በላይ የተቀበሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ክስ መሰረተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዐቃቤ ህግ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሺ ባልሆኑ ሰዎች ስም ከ65 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ካሳ የተቀበሉ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ ክስ መሰረተ፡፡
በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ በማጠናቀቅ አመራሮቹ በከባድ የሙስና ወንጀል ስር ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ክስ የተመሰረተው የልማት ተነሺ ባልሆኑና እስካሁን ትክክለኛ ማንነታቸው ባልታወቁ 21 ግለሰቦች ስም 65 ሚሊየን 977 ሺህ 620 ብር ካሳ ከመንግስት በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ወረዳ ስራ አስፈጻሚ እና የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎችን ጨምሮ በ21 ግለሰቦች ላይ ነው፡፡
በዛሬው ዕለትም ክሱ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተልኮ እና ተከፍቶ ችሎቱ መሰየሙ ተመላክቷል፡፡
በዚህ መሰረት ዐቃቤ ሕግ የመሰረተው ክስ በችሎቱ ለቀረቡት ተከሳሾች እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፥ በችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾች ክሱ ደርሷቸው ለሁሉም ተከሳሾች ክሱን ለማንበብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ የተመዘበረውን የህዝብ ሀብት ለማስመለስ ያስችል ዘንድ የተለያዩ ቤቶች፣ ሕንጻዎች፣ በባንክ የሚገኙ ገንዘቦች፣ ተሽከርካሪዎች እና የግንባታ ማሽነሪዎችን እንዲታገዱ መደረጉን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!