Fana: At a Speed of Life!

በሩሲያ-ዩክሬን ቀውስ በመከረው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ወንበሯን ባዶ በማድረግ ስብሰባውን ማለፏ በበሳል የዲፕሎማሲ ውሳኔ የተደረገ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ-ዩክሬን ቀውስ ላይ በመከረው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ወንበሯን ባዶ በማድረግ ስብሰባውን ማለፏ በበሳል የዲፕሎማሲ ውሳኔ የተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የሩሲያ – ዩክሬን ግጭትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩን ከሌላው የሚለየው ከግጭቱ ጀርባ ያሉ ሃይሎች ማንነት መሆኑን ጠቅሰው፥ ግጭት ውስጥ ያሉት አካላት ኒውክሌር የታጠቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህ ጦርነት አሸናፊ የሚሆን የለም ያሉት ቃል አቀባዩ ሁለቱም አካላት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ መጠየቋን አስታውሰዋል።

በሁለቱ ወገኖች ቀውስ ላይ በመከረው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ወንበሩን ባዶ በማድረግ ስብሰባውን ማለፏም በበሳል ዲፕሎማሲ የተደረገ ውሳኔ መሆኑን ጠቁመው÷ የሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ጥቅሟን የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው÷ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በፖለቲካ እና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ወዳጅነቷን አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ ዴቪድሰን ገለጻ መደረጉን አውስተዋል።

ኤች አር 6600 የቆየውን የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የማይመጥን እንደሆነ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኩል ገለጻ እንደተደረገላቸውም አንስተዋል።

 

የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ ዴቪድሰንም አገራቸው ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ማድነቃቸውንና አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኘነቷን ማጠናከር እንደምትፈልግ መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ለሊባኖስ መንግስት የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በአረብ አገራት ዙሪያ የሚስተዋለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከሁለትዮሽ እና የንግድ ግንኙነት ጋር በተያያዘም የጂቡቲን የካርጎ አገልግሎት ማፋጠን የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም ከቱርክ ጋር በንግድ እና በኢንቨስትመንት ግንኙነትን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ተካሂዷልም ብለዋል።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘም ዜጎችን ከሳዑዲ ለመመለስ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በመግለጫው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመደጋገፍ ግንኙነታቸውን እያሳደጉ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፥ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አጋርነታቸውን እያሳዩም  ነው ተብሏል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለአካባቢው ሰላም እና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ዲና፥ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ሁኔታ በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ የተወሰነ እንቅፋት መፍጠሩንም አመላክተዋል።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ጥቅሟን የሚያስጠብቅ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ የአምባሳደሮችን አመዳደብ በተመለከተ ኢትዮጵያ ከየአገራቱ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተቀማጭ በሆኑ፣ ተቀማጭ ባልሆኑ እና በአነስተኛ የሰው ሃይል በሚደገፉ አምባሳደሮች ለማከናወን ወስና እየተንቀሳቀሰች ነው ብለዋል።

ጂ ፎር የተሰኘው የኢትዮጵያ፣ የናይጀሪያ፣ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ስብስብ አዲስ ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቅሰው÷ ከሌሎች አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ተቋማት ጋር የሚጣረስ ነገር እንደሌለውም ነው ያነሱት።

በወንደሰን አረጋኸኝ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.