Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ኢንዱስትሪዎቿ የካርበን ልቀትን እንዲቀንሱ የምታደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ኢንዱስትሪዎቿ የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን እንዲቀንሱና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎች መቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡
በቻይና ህዝባዊ ብሄራዊ ኮሚቴ አምስተኛ የፖለቲካ ምክክር ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው፥ ሀገሪቱ ለበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ እና በሀይል ምንጯ ላይ ሽግግር ለማምጣት ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ተገልጿል፡፡
ባለፈው ዓመት የቻይና ብሄራዊ ባንክ የድንጋይ ከሰል አጠቃቀምን ለሚያሻሽሉ ስራዎች አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ፖሊሲ ያወጣ ሲሆን፥ ይህም ድጋፍ 31 ነጥብ 66 ቢሊየን ዶላር እንደሚሆን ነው የተጠቆመው።
የሻንጋይ የህዝብ ባንክ ዋና ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ጂን ፔንግሁዊ እንዳሉት፥ ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ በየዓመቱ ወደ ከባቢ ዓየር ከሚለቀቀው የበካይ ጋዝ መጠን ውስጥ 40 ሚሊየን ቶን በላዩን የሚቀንስ ሲሆን፥ በመላው ሀገሪቱ ሲተገበር አሃዙ 110 ሚሊየን ቶን ካርበን ይሆናል።
በተጨማሪም ከንፋስ እና ፀሐይ ሀይል የማመንጨት አማራጮችን ለሚጠቀሙትም የፋይናንስ ድጋፉ እንደሚደረግም ተመልክቷል።
ቻይና በስፋት በድንጋይ ከሰል ላይ የተመሰረተውን የሀይል አቅርቦቷን ለማሻሻል በመስራት ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2005 ላይ 72 ነጥብ 4 በመቶ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ድርሻ በ2020 ወደ 56 ነጥብ 8 በመቶ ማውረዷን ነው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ የሚያመለክተው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.