Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉን የምጣኔ ሐብት ቀውስ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ቁጠባ ላይ ማተኮር አለባት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሐብት ቀውስ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቁጠባ ላይ ማተኮር እንዳለባት ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አማካሪ የሆኑት ዶክተር አህመድ አብዱራህማን ተናገሩ።

ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አማካሪው ዶክተር አህመድ አብዱራህማን ÷ ከተጀመረ ሁለት ሣምንታት ያስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከወታደራዊነቱ ውጊያ ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የኢነርጂ ፍልሚያን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት በተለይም የዓለምን የኢኮኖሚ ቀውስ አባብሶታል ነው ያሉት።

ለዓለም ገበያ 30 በመቶ የስንዴ ምርት በምታቀርበው ሩሲያ እና በስንዴ ምርት አቅርቦት የምትጠቀሰው ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸው ደግሞ የምግብ እህል ግብይቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረ ነው የተናገሩት፡፡

የበቆሎ ምርት ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡት ሀገራት ሩሲያ 19 በመቶውን እንደምትሸፍን ያነሱት ዶክተር አህመድ፤ የዓለምን የሱፍ ዘይት ገበያ አብዛኛውን ድርሻ የተቆጣጠሩትም ሩሲያና ዩክሬን መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዓለም አቀፍ የግብይት ቋቶች መረጃ መሰረት ዩክሬን ለዓለም ገበያ ከ46 በመቶ በላይ፣ ሩሲያም ከ25 በመቶ ያላነሰ የሱፍ ዘይት ያቀርባሉ።

በየቀኑ ሩሲያ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ የነዳጅ ዘይትን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ መሆኗ የዓለምን የነዳጅ ዘይት የገበያ ዋጋ በበርሜል ከነበረበት 80 ዶላር አሁን ወደ 140 ዶላር አድርሶታል።

ለግብርና ሥራ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን “ዩሪያ” እና “ዳፕ” የተባለ የአፈር ማዳበሪያ የ15 በመቶ፣ ለቀይ አፈር የሚሆን ፖታሽ ማዳበሪያን ደግሞ የ17ውን ሽፋን ወስዳ የምታቀርበው ሀገር ሩሲያ መሆኗንም አንስተዋል።

ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ እንዳይቀርቡ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ጫና በመፈጠሩና የምርት ሂደትንም በማስተጓጎሉ በተለይም በማደግ ላይ ላሉ አገራት ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።

የሁለቱ ሀገሮች ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በተለይም የስንዴ ምርት አቅርቦት ላይ ጫና ይኖረዋል ብለዋል።

ሁለቱ ሀገሮች የሱፍ ዘይት በስፋት የሚመረትባቸው ሀገራት በመሆናቸው የሰሊጥና የኑግ ዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት ፈጥሯል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው በብዛት የግብርና ምርቶችን በመሆኑና የምርቶቹ አብዛኛው መዳረሻ አውሮፓ ከጥሬ እቃ ግብይት ይልቅ ጦርነቱ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ጫና ይኖረዋልም ነው ያሉት።

በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ ለጦርነት ተፈናቃዮችና መልሶ ማቋቋሚያ በማዋል ታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመቋቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት መስራት አለባት ብለዋል።

ከጦርነቱ ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውና በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት ካላቸው ቱርክ እና ቻይና ጋር ያለውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በተለይም በከተማ ግብርና ሁሉም ቤተሰብ አተኩሮ እንዲሰራና መንግስት እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብ በትጋት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን እየተገበረው ያለው የበጋ መስኖ ልማትን ማጠናከርም ሌላኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጦርነቱ ጫና ለኢትዮጵያም ፈታኝ በመሆኑ ችግሩን በትብብርና አንድነት ለመሻገር ህዝብና መንግስት እጅ እና ጓንት ሆነው መስራት አለባቸው ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የመንግስት አስተዳደር እና ህዝቡ በጋራ የሚቆሙበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ዶክተር አህመድ፤ ከነዳጅ ምርት ጀምሮ ወጪ ቁጠባ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ በሆነ መልኩ ገንዘባቸውን ወደ ሀገር ቤት በመላክ መንግስትና ህዝባቸውን ማገዝ አለባቸው ሲሉም ለኢዜአ ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.