ኬንያ በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቀች
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጠየቁ፡፡
ፕሬዚዳንት ኬንያታ በቤተመንግስታቸው ከዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሃገሪቷን እየጎዳ በመሆኑ ሊነሳ ይገባል።
በሃገሪቱ ላይ የተጣለው ዕገዳ አግባብ አለመሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ማእቀቡ እንዲነሳ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገራቸውም ሃገሪቱ ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ የምታደርገውን ክትትል እና ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
በአሜሪካ እና የተወሰኑ ምዕራባውያን ሃገራት በፈረንጆቹ 2003 በዚምባብዌ የምርጫ መጭበርበር እና ሰብአዊ መብት ረገጣ ተፈጽሟል በሚል ማዕቀብ እንደተጣለባት ይታወሳል።
የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው፥ ምዕራባውያን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በሃገሪቱ የተገበሩት የመሬት አያያዝ ማሻሻያ ፕሮግራም ነጭ ገበሬዎችን አፈናቅሏል የሚል ውንጀላ እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ።
በዚህ ሰበብ ምክንያትም ሃገራቸው ላይ የበቀል እርምጃ እየተወሰደባት ነው፤ ይህም አግባብ አይደለም ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ህልፈት በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ዚምባብዌ ከምዕራባውያን ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ይነገራል።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የመንግስትነት ዘመንም የዚምባብዌ ሁኔታ አልተለወጠም እንደሚል ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!