Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለምታካሂደው አገራዊ ምክክር ስኬታማነት የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ- ፈረንሳይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው አገራዊ ምክክር ስኬታማነት የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሹ ገለጹ።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበትን 125ኛ ዓመት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው አገራቱ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን ገልጸው÷ግንኙነቱ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዳለውም ተናግረዋል።
አገራቱ በምጣኔ ሃብት ረገድ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቀሱት አምባሳደሩ÷ በአሁኑ ወቅትም ፈረንሳይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ 438 ሚሊየን ዩሮ ፈሰስ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።
ጎን ለጎንም 58 የፈረንሳይ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥረው የኢንቨስትመንት ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል 8 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው÷ አሁን ላይ ደግሞ ለመጀመሪያ ዙር 10 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ፈረንሳይ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትም ለኢትዮጵያ እያቀረበች መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፥ ላሊበላን ጨምሮ በተለያዩ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ላይ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑንም አስረድተዋል።
አገራዊ ምክክሩን በተመለከተ እስካሁን መንግሥት የድጋፍ ጥያቄ አለማቅረቡን ጠቁመው፥ በቀጣይ ጥያቄ ካቀረበ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1897 የፈረንሳዩ ልዑክ ከአጼ ምኒልክ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ፈረንሳይ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ግንባታ፣ በባቡር መሰረተ-ልማት፣ በሕንጻ ግንባታ፣ በሙዚቃና በፊልም ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም በሥነ-ጽሁፍ አስተዋጽዖ ማድረጓ ተገልጿል፡፡
ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የነበሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በርካታ ኢትዮጵያውያን የፈረንሳይኛ ቋንቋ አቀላጥፈው መናገራቸውም ለሁለቱ አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተመልክቷል።
በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የቋንቋ መስተጋብርም በተለይም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ቋንቋ ውርርስ እንዲኖር በማድረግ በተለይም የነገሮች ስያሜ በፈረንሳይኛ ስሞች ጸንቶ እንዲቆይ በማስቻሉም ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.