Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና በሚያካሂደው ጉባዔ ለሃገርና ህዝብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጡ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ ይገባል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በሚያካሂደው ጉባዔ ለሚስተዋሉ የሃገርና ህዝብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጡ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ ይገባል ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡

ፓርቲው በጉባዔው ለሰላምና ደህንነት ብሎም ህዝብን ለምሬት ለዳረጉ የኑሮ ውድነትና ለብልሹ አሰራሮች መፍትሄ ማስቀመጥ እንዳለበትም ነው ምሁራኑ የጠቆሙት፡፡

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሱራፌል ጌታሁን÷ ጉባዔው ሃገር በተለያዩ ችግሮች ባለችበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ፓርቲው ለእነዚህ ችግሮች ወሳኝ መፍትሄ የሚሰጡ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በፈተናዎች ውስጥ ለሆነች ሃገር ከፈተናዋ የሚያሻግሩ ሀሳቦች እንደሚጠበቁም ነው መምህሩ የገለጹት፡፡

የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሃይለየሱስ ታየ በበኩላቸው÷ ፓርቲው ሃገርን ከገጠማት ችግር የሚያሻግሩ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፍ የሚጠበቅ እና ለህዝብ ችግሮች መፍትሄ ማስቀመጥ ያለበት ጉባዔ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለምታደርገው ሃገራዊ ምክክር የሚበጁ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ አንደሚጠበቅ ምሁራኑ አንስተዋል፡፡

ህዝብን ለምሬት የዳረጉ፣ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ግለሰቦች በፓርቲ ውስጥ ተሸሽገው እንደሚኖሩ ጠቅሰው÷ ለህዝብ እንግልት ምክንያት የሆኑትን የሙስናና ሌብነት ተዋንያንን ፓርቲው ሊያጠራ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሙስና ተዋንያን የፓርቲው አመራሮችና አባላትን በመለየት ብልፅግና እርምጃ መውሰዱ ራሱንም ሀገርንም ይታደጋል ያሉት ምሁራኑ÷ ከዚህ በፊት እንደሚስተዋለው ቦታ መቀያየር ሳይሆን ፖለቲካዊና ህጋዊ ተጠያቂነትን ማስፈን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ህዝብን ለምሬት የዳረጉ እና በአሻጥር የምጣኔ ሃብት ኪሳራ ያደረሱት ላይ ፖለቲካዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ምሁራኑ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.