የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤውን ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ያካሂዳል።
ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በሚጀምረው ጉባኤው የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ አስታውቋል።
ጉባኤውን አስመልክቶ የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ፥ የብልጽግና አንደኛ ጉባኤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፓርቲው በሁሉም መስክ የተጎናጸፋቸውን ድሎች እንደሚገመግም ተናግረዋል።
ፓርቲው የገጠሙትን ችግሮች እና ተግዳሮቶች በጥልቀት ገምግሞ ለማረም ታሪካዊ ውሳኔ ያሳልፋልም ነው ያሉት።
ጉባኤው በጸጥታ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክርም ገልጸዋል።
በዚህም ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያመጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ነው ያስታወቁት።
በጉባኤው 1 ሺህ 600 የፓርቲው አባላት በድምፅ የሚሳተፉ ሲሆን፥ 400 ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ እንግዶች ያለ ድምፅ ይሳተፋሉ ።
ጉባኤው የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት የሚጎናጸፉበት፣ ፓርቲው በአደረጃጀት እና አሰራር ራሱን የሚያጠናክርበት እንዲሁም ፓርቲውን ሊያሻግሩ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጠንካራ የፓርቲ አመራሮች የሚመረጡበትም ይሆናል ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ የቅድመ ጉባኤ መድረክ በትናንትናው ዕለት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በማጠቃለያ መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን ከዚህ ቀደም በሀገራችን የሰራነውን የማፍረስ፣ አንድ ከሚያደርጉን ይልቅ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት እንዲሁም ገቢራዊነት መጓደልና ግለሰቦች ከሀገር በላይ የሆኑበት ሁኔታዎች ይስተዋሉ ነበር ብለዋል፡፡
ብልጽግና እነዚህን ችግሮች በሚፈታ መልኩ እየተጓዘ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ከስርዓትና ከተልዕኮ አፈፃፀም ጋር የሚያያዙ ችግሮችን መፍትሄ በመስጠት እንዲሁም ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የፓርቲውን የአጭር ጊዜ እቅዶችና የረጅም ጊዜ ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የብልፅግና ፓርቲ በሚያደርገው አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ለመታደም የውጭ አገራት እህት ፓርቲዎች ልዑካን አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!