Fana: At a Speed of Life!

አጋር በሚል ስንገፋ የቆየን ድርጅቶች አሁን የውሳኔ ሰጪነት ዕድል አግኝተናል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አጋር ፓርቲ በሚል ስንገፋ የቆየን ድርጅቶች አሁን የውሳኔ ሰጪነት ዕድል አግኝተናል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ርዕሠ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት “አጋር ፓርቲ ናችሁ” በሚል ሰበብ በኢህአዴግ ጉባዔዎች እንዳንሳተፍ ስንገለል ቆይተናል ብለዋል።

አጋር ተብለን ስንገለል የነበረበት የፖለቲካ አካሄድ አንዱን ቤተኛ ሌላውን ባይተዋር ያደረገ አሰራርን የሚከተል እንደነበር አውስተው÷ ከዚህ ቀደም በነበረው ስርዓት በአብዛኛው ድንበር ላይ የምንገኝ ክልሎች እኛ እናውቅላችኋለን በሚሉ አምባገነኖች ምክንያት ወሳኝ አገራዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳንገኝ በህግ ተከልክለን ቆይተናል ነው ያሉት፡፡

አንድ አገር ላይ ሆነን ስለእኛ ሌላ አካል እንዲወስንልን መደረጉ ስህተት ቢሆንም ያሉት ርዕሠ መስተዳድሩ÷ ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጀምሮ አሰራሩን በመቀየር በፓርቲው ውስጥ በሚነሱ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነቱን ዕድል ሁሉም ክልል እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።

ይህም የውሳኔ ሰጪነት አቅማችንን በአግባቡ እንድንጠቀም በር ይከፍታልም ነው ያሉት።

ብልጽግና ፓርቲ አጋርና ዋና የሚለውን በማስቀረቱም ሁሉን አሳታፊና አካታች መሆኑን በተግባር አሳይቷል ያሉት አቶ አሻድሊ÷ ብልጽግና እንደከዚህ ቀደሙ በወሳኝ የፓርቲ ጉባኤዎች ላይ አንተ ዳር ሆነህ ታያለህ፣ አንተ ትሳተፋለህ የሚል አሰራር የለውም ብለዋል።

ሁሉንም አባል ፓርቲዎቹን አካቶ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሃሳብና ውሳኔ የምንሰጥበትን መድረክ ፈጥሯል ብለዋል።

በብልጽግና ጉባኤ ተመልካች ሳይሆን ዋና ተዋናይ ሆነው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸው÷ ይህ ለአገራችን የፖለቲካ ስርዓት ትልቅ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አሳታፊነቱ ይበልጥ እንድንሰራና ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ እንድንቀርፍ ዕድል የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ÷ የሰሚ ሰሚ ከምንሰማው ይልቅ እራሳችን ወሳኝ በሆነው የፓርቲያችን ጉባኤ ላይ የሚወጡ የውሳኔ ሃሳቦችም ለችግሮቻችን መፍትሄ እንደሚሆኑ እናምናለን ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በእኩልነትና በፍትሀዊነት ላይ የጋራ ዕምነት ያላቸው ፓርቲዎች ተዋህደው የመሰረቱት አገራዊ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን አመልክተው÷ ይህን ፓርቲ ይበልጥ አሳታፊነቱን እያጠናከረ እንዲሄድ ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.