ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም፣ ፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚሰራ እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ነው- አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ “ከፈተና ወደ ልዕልና!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባኤው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ÷ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም፣ ፍትህ፣ የልማት እና መልካም አስተዳደር ፍላጎት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑትን የወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴቶችን እና የዴሞክራዊ ባህልን ለማጎልበት የሚታገል እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ ጀምሮ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ዜጎችን ባሳተፈ መልኩ በብቃት እየተሻገረ ትምህርት እየወሰደ እና ችግሮችን ወደ ድል እየቀየረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ያለፉትን ጠንካራ ጎኖች እና ጉድለቶች በየፈርጁ በመለየት ለቀጣይ ትውልድ ዘላቂ ጥቅም የሚተጋ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲው በኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጠውን አደራ በብቃት ለመወጣትም የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በሚገባ ፈትሾ በማጥራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ሰፊ የማጥራት ስራ ተጀምሯል ያሉት አቶ አደም÷ በዚህም በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ጉባኤ የፓርቲውን አመራር እና አባላት ጥራት የማሳደግ ስራ የሚያጠናክሩ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ይወሰናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡
የፓርቲው ጉባኤ ዓላማ እንዲሳካ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ