Fana: At a Speed of Life!

የቻይናና ሩሲያ ገዢ ፓርቲዎች ለብልፅግና ፓርቲ ስኬታማ ጉባኤን ተመኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ እና የሩሲያው ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ትናንት አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ለጀመረው ብልፅግና ፓርቲ የተሳካ ጉባኤን ተመኙ።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ ለፓርቲው በላከው መልዕክት ለጉባኤው ስኬት ምኞቱን ገልጿል።

ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት ጠቃሚ ነው ያለው ፓርቲው፥ ይህን ግንኙነት አዳብሮ ለቀጣይ የልማት አጀንዳዎች ለማዋል ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመስረት ዝግጁ መሆኑን ነው ያረጋገጠው።

በጥቅሉ የቻይና እና ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ትብብር የበለጠ እንዲጠናክር የሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ መስራት ጠቃሚ መሆኑም በመልዕክቱ ተነስቷል።

በተመሳሳይ ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ለብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በላከው መልዕክት በጉባኤው ኢትዮጵያውያንን የሚጠቅም ወሳኝ እና ጠቃሚ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት እምነቱ መሆኑን አስታውቋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ወዳጅ ፓርቲ መሆናቸውን ያነሳው መግለጫው፥ ይህም ወዳጅነት በፓርቲዎቹ መካከል በተገቡ የትብብር ስምምነቶች የጠነከረም እንደሆነ ነው ያመለከተው።

ይህ የሁለቱ ፓርቲዎች ትብብር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ በመስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቱን ገልጿል።

ሩሲያ፥ በአፍሪካ ኢትዮጵያን አስተማማኝ አጋር ሀገር አድርጋ እንደምትወስድ በመጠቆምም ሀገራቱ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ወይም የሚመሳሰል አቋም ማንፀባረቃቸውም የዚህ ማሳያ ነው ብሏል።

አያይዞም በፊታችን የፈረንጆቹ ግንቦት ወር በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ገዢ ፓርቲዎች ፎረም ላይ ብልፅግና ፓርቲ እንዲሳተፍ ግብዣ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.