Fana: At a Speed of Life!

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስክሬን የሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስክሬን የሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አባቶች እና የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የሽኝት መርሃ ግብሩ የተካሄደው፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የውጪ አገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ለአገራቸው በየደረጃው ከልጅነት እስከ እውቀት የሚገባቸውን ሁሉ አግልግሎት ማበርከታቸውን አውስተዋል፡፡

ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብሎም ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ሲሰጡ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስተመጨረሻ በአርምሞ እና በጸሎት መኖራቸውን ጠቁመው፥ አሁን ላይም ከጠፊው ዓለም ወደ ዘላለማዊው ዓለም በክብር ተሻግረዋል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ምድር በርካታ ፈተናዎችን እያሳለፈች ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ በዚህ ሁሉ መሃልም አቡነ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በህይወት ዘመናቸው እግዚአብሄር የሚወደውን ሁሉ አድርግረዋል፤ በረከታቸውን እና ረድኤታቸውን ያሳድርብን ሲሉም አውስተዋል፡፡

በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስክሬን ሽኝት ስነ ስርዓት ከቤተክርስቲያን ጎን በመሆን በመርሃ ግብሩ ለተሳተፉ እና ለተገኙ አካላት ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቤተክርስቲያኗ ትምህርት የሆኑትን አቋቋም፣ ድጓና ዝማሬ መዋስዕት በላቀ ሁኔታ የተማሩ መሆናቸውን የሕይወት ታሪካቸው ይናገራል።

ብጹዕነታቸው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ84 ዓመታቸው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ማረፋቸው ይታወሳል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ስነ ስርዓት ነገ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.