አምስቱ “የጀነሬሽን አንሊሚትድ” ዓለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ የንግድ ሃሳቦች ተለዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አምስቱ የጀነሬሽን አንሊሚትድ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ የንግድ ሃሳቦች መለየታቸውን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች ለማበረታታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ባከናወነው የ2014 ዓ.ም የጀነሬሽን አንሊሚትድ ለውጥ አምጪ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ውድድር አምስት አሸናፊ ቡድኖች መመረጣቸውን አስታውቋል፡፡
የውድድሩ ተልዕኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ወጣቶችን ከተለያዩ ዕድሎች ጋር ማገናኘት ሲሆን÷ በዚህ ውድድር ከተለዩት የመጨረሻዎቹ ሁለት ቡድኖች ዓለም አቀፉን ውድድር እንደሚቀላቀሉም ተመላክቷል፡፡
በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአጋርነት እና ፈንድ ዳይሬክተር አቶ ጥዑመዝጊ በርሔ÷ ውድድሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዕድሉ ከተመቻቸላቸው በርካታ ችግር ፈቺ ሃሳቦች እንዳላቸው ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል፡፡
ውድድሩ በ40 ሀገራት መካከል የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ በኢትዮጵያ 5 ከተሞች ተከናውኖ በ8 ሣምንታት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
አሸናፊ ሆነው የተመረጡት÷የእንስሣት መኖ የማምረት፣ ከቀርከሃ ውሃ የማጣራት፣ ኮዲንግ፣ በማሽን ጥለት የመሥራት እና ለህክምና የሚረዳ የመተንፈሻ መሳሪያ የመፍጠር ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆኑ÷ ሥራ ፈጣሪነት፣ ገበያ ማግኘት፣ ችግር ፈቺነት እና የፈጠራ ሃሳቡ አዲስነት ከመመዘኛ መስፈርቶቹ ውስጥ መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውድድሩ 700 ሃሳቦች እንደቀረቡ የጠቀሱት አቶ ጥዑመዝጊ÷ አሸናፊ የሆኑትን አምስቱን ለመምረጥ የነበረውን ፈታኝ ሂደትም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!