Fana: At a Speed of Life!

አሁን እየታየ ያለው የሙቀት መጠን በበልግ ወቅት የሚጠበቅ ነው – የሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የበልግ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት መሆኑንና አሁን እየተስተዋለ ያለው ነገር ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩት ገለፀ፡፡

የኢኒስቲቲዩቱ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም በበልግ ወቅት የዝናብ ተጠቃሚዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖርና በሙቀቱ ምክንያት በውሃ አካላትና ግድቦች ላይ ያለው የትነት መጠን እንደሚጨምር ገልፀዋል፡፡

በበልግ ወቅት እየታየ ያለው የዝናብ ስርጭት በአመዛኙ ከመደበኛ በታች እንደሆነና የተወሰነ ዝናብ ዘንቦ በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ጸባይ እየተስተዋለ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩት ትንበያ መሰረት ከፈረንጆቹ መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የበልግ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከበልግ ዝናብ ሽፋን አኳያ አብዛኛው የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ያገኛሉ ብለዋል።

የበልግ ወራት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም የደቡብ ከፍተኛ ቦታዎችና ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም አብራርተዋል።

ከፈረንጆቹ መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች የደመና ክምችቱ እየተጠናከረ በመምጣት መጠነኛ እርጥበት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ እርጥበቱን በአግባቡ እንዲጠቀም ጠይቀዋል።

በበልግ ወቅት ከመደበኛው በታች ዝናብ የሚያመዘን በመሆኑ በውሃ አካላትና በግድቦች ያለውን ውሃ በአግባቡ መጠቀምና በአጠቃላይ ውሃን በጥንቃቄ መያዝና ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ አቶ አህመዲን ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.