Fana: At a Speed of Life!

የሰከላ-አዴት የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ፕሮጀክት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው 61 ኪሎ ሜትር የሰከላ- አዴት የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በጥሩ የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡

እስከ አሁን ባለው የስራ እንቅስቃሴም የአፈር ቆረጣና ሙሌት ሥራ፣ የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች በጥሩ ደረጃ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

መንገዱ ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ለመንገዱ ተጠቃሚ ህብረተሰብ የትራንስፖርት መስተጓጎል እንዳይደርስበት ለማድርግ የተለዋጭ መንገድ ግንባታ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የመንገድ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው አገር -በቀሉ ዲ.ኤም.ሲ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን÷ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው።

ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው 2 ቢሊየን 578 ሚሊየን 671 ሺህ 578 ብር የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑ ታውቋል፡፡

መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ለስራ ተቋራጩ የሶስት ዓመት የጊዜ ገደብ የተሰጠው ሲሆን÷ ግንባታው በተገቢው የጥራት ደረጃ እና ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በአትኩሮት እየተሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

መንገዱ ትከሻን ጨምሮ በከተማ 21 ሜትር ፣ በቀበሌ እና በገጠር ደግሞ 10 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ከመንገድ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አካባቢው የጤፍ ፣ ስንዴ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ማርና የአትክልት ምርታማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ የፕሮጀክቱ ግንባታ መጠናቀቅ ሚናው የጎላ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.