የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በራስ አቅም ብቻ ማደግ እንደሚቻል ማሳያ ነው- አቶ እርስቱ ይርዳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ ወቅት በመስኖ የተጀመረው የስንዴ ሰብል ልማት ጅምር አመርቂ ውጤት ባለን የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የሰው ኃይል ብቻ መለወጥ እንደምንችል ያረጋገጠ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡
በርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ የተመራ ልዑክ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የተፋሰስና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጎብኝቷል፡፡
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር÷ የመለወጥ ጽኑ እምነት ይዘን ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በተቀናጀ መንገድ በማልማት ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንችላለን፤ ለዚህም የህዝቡን ጉልበት፣ ሙያ፣ ልምድና ተነሽነት በአግባቡ መምራት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ያየነው የስንዴ ልማት አቅምና ሰፊ እድል እንዳለን ያረጋገጠ በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ወኔ ሰንቀን መስራት ይገባናል፤ አርሶ አደሩም ጅምሩን እንዲያሰፋ፣ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት በማምረት የሀገር አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድሩ የተፋሰስ ልማትን የጎበኙ ሲሆን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ በብዙ አካባቢዎች የሚታየውን ከተዳፋትነት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የአፈር መሸርሸር ችግር ለመቅረፍ ህብረተሰብ አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ይገባል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ በዚህ ዓመት በተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስከ 200ሺህ ኩንታል የሚሆን ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው÷ ጅምር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የስራና ቁጠባ ባህልን በመለወጥ፣ የጊዜ፣ የጉልበትና የምርታማነት አጠቃቀምን በማጎልበት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በጉራጌ ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ሺህ 200 ሄክታር በበጋ መስኖ በስንዴ ሰብል የለማ ሲሆን፥ በህዝብ ተሳትፎ 100 ሺህ ሄክታር መሬት በተፋሰስ ንቅናቄ መልማቱም ተመላክቷል፡፡
በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳን ጨምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዲሁም የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡