የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጠመንጃ መፍትሄ አይሆንም- የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጠመንጃ መፍትሄ አይሆንም ሲሉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ገለጹ፡፡
አቶ ሙላቱ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ፓርቲያቸው አሁን ዓለም የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከምስረታው ጀምሮ ሰላማዊ ትግል እያካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኦሮሚያ ሰላም ስትሆን ኢትዮጵያም ሰላም ትሆናለች ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፥ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እና ፍትህን ለማስፈንም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ለሀገር እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንጂ ጠመንጃን እንደ መፍትሄ መጠቀም ጊዜው የማይፈቅድ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አሁን ላይ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ችግሮች የሚስተዋሉ መሆኑን አቶ ሙላቱ አንስተዋል፡፡
በአንጻሩ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለው ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑንም አውስተዋል፡፡